1ኛ ለወጣ 50 ሺህ ብር የሚያስገኝ የአሸናፊዎች አሸናፊ ሀገር አቀፍ የሒሳብ የትምህርት ውድድር ሊካሄድ ነው፡፡

“የሂሳብ ትምህርት ይከብዳል” የሚል የተሳሳተ አመለካከት በማስወገድ “ጉብዝና ያሸልማል” በሚል መሪ ቃል የ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የሒሳብ የትምህርት ውድድር የመዝጊያ መርኃግብር በአዲ አበባ ሊካሄድ መሆኑ ተነግሯል።

በኢትዮጲያ ብቸኛው የሆነው የሒሳብ ትምህርት አወዳዳሪ ተቋም ማይሶሮባን ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር ከ አንድ ደቂቃ ጋር በመሆን፤ ሀገር አቀፍ የትምህርት እና የስሌት ውድድር በሀገራችን በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መዘጋጀ ተገልጿል።

ተቋሙ መጠሪያ ስያሜውን ያገኘው ከጃፓንኛ ቃል ሲሆን፤ ትርጓሜውም አባከስ ማለት መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ አጥናፉ በዛሬው ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ውድድሩ የሚከናወነው ከ3 እስከ 12ተኛ ክፍል ድረስ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ የሚፈተኑበት ቋንቋ መንግስት ባዘጋጀው መማሪያ መፀሀፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን እና 30 ሺህ የሚሆኑ ፈታኞች መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል።

ስድስት ዙሮች ያሉት ውድድሩ ፤ አምስቱ ዙሮች በየከተሞቹ የተከናወኑ ሲሆን የመጨረሻው እና የስድስተኛው ዙር የፍፃሜ ውድድር፤ የየከተማው አሸናፊ ተማሪዎች በተገኙበት ከሀምሌ 26 እስከ ነሀሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው፤ በሚሊኒየም አዳራሽ ይወዳደራሉ ተብሏል።

የአሸናፊዎች አሸናፊ ተማሪዎች ተለይተው ለአህጉር እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ተነግሯል።

የመጨረሻ ዙር የአሸናፊዎች አሸናፊ በውድድር ስነ ስርዓቱ ላይ 4 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ የገንዘብና የአይነት ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤ 1ኛ ለወጣ ለአሸናፊዎች አሸናፊ 50 ሺህ ብር የሚሸለም ሲሆን፤ 2ተኛ እና 3ተኛ ለወጡ አሸናፊዎች የ45 እና 40 ሺህ ብር ተሸላሚ ይሆናሉ ተብሏል።

ተቋሙ በ2016 ዓም ሀገር አቀፍ የሒሳብ ትምህርት ውድድር፤ ከ50 ከተሞች በላይ የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እና ከ3 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማሳተፍ መቻሉ ተጠቁሟል።

በዕለቱ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኮሜዲያን ቤቲ ዋኖስ የማይሶሮባን ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በጎ ፈቃደኛ የክብር አምባሳደር ሆና ተመርጣለች።

በእሌኒ ግዛቸው

ሰኔ 06 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply