12 አገር በቀል የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በስራቸው ሳቢያ ከመንግስት ጫና እና እንግልት እየጠነከረባቸው እንደሆነ አስታወቁ

👉🏿 የሲቪክ ምህዳሩ ዳግም ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እየተመለሰ ነው

ሰኔ 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሞያዎች ማህበር እና ሌሎች 9 አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ በመሆን በሰብዓዊ መብት ላይ በሚሰሩ ድርጅቶች ላይ መንግስት እያደረሰ የሚገኘውን ጫና እና እንግልት ገልጸው ለስራቸው አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን አሳስበዋል።

የሰብዓዊ መብቶችን ዋና ትኩረት አድርገው የሚሰሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ የሚታዩ ጉልህ ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት የሰሉ አስተያየቶችን እና የእርምት እርምጃ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በመለየት ጠንካራ የውትወታ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።

ነገር ግን በአንዳንዶቹ ማህበራት ላይ ከመንግስት በኩል ተደጋጋሚ ጥቃትና ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው እንደሚገኝ 12 ድርጅቶች በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም መሰል ጫናዎች በሕጎች፣ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ጭምር እየተደገፉ መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ አመላክተዋል። በመሆኑም በመንግስት በኩል እየተፈጸሙ ያሉት ክልከላዎች፣ ጫናዎችና ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሆናቸውን ድርጅቶቹ ጠቁመዋል።

የመንግስት ጫናዎች በአይነት እና ባህሪያቸው እንዲሁም መጠናቸውን በመቀያየር መከሰታቸው ተስፋ ታይቶበት የነበረው የሲቪክ ምህዳር ዳግም ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መመለሱን አመላካች ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

እየደረሱ ካሉ ጫናዎችም ውስጥ በአንዳንድ የድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች፣ በቦርድ አመራሮችና በሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የሆኑ ማስፈራሪያዎች፣ ዛቻዎችና ጫናዎች ተፈጽመዋል፤ አሁንም እየተፈጸሙ ነው የተባለ ሲሆን ሕገወጥ እና የዘፈቀደ እስራት እንዲሁም የቢሮ ሰበራዎች እና ንብረቶችን የመውሰድ ድርጊቶች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

ይህን ተከትሎ ሁሉም የመንግስት አካላት እየደረሰ ያለውን ጥቃት እና ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥቃቱን የሚፈፅሙትን ሕገወጥ አካላት ተጠያቂ በማድረግ ለሲቪል ማኅበራት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም መንግስት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ሲቪል ማኅበራት በነጻነት ከስጋት ውጪ ሆነው ስራቸውን መስራት እንዲችሉ ምቹ የሆኑ የሕግና የፖሊስ ማዕቀፎችን በመዘርጋት የሲቪል ምኅዳሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያስቆም አሳስበዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply