3 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ይልቅ ለብድር ወለድ ከፍተኛ ገንዘብ በሚከፍሉ አገራት እንደሚኖር ተገለጸ

ከዓለም ሕዝብ ግማሽ ያህል የሚጠጋው (3 ነጥብ 3 ቢሊዮን) ሕዝብ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ከሚያወጡት ገንዘብ ይልቅ፤ በተለይም ከሀብታም አገራት ለተበደሩት ብድር ከፍተኛ ወለድ በሚከፍሉ አገራት ውስጥ እንደሚኖር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚሆን ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቋል ማለቱን አዲስ ማለዳ ባለፈው ዕሮብ ይፋ በተደረገው መረጃ ላይ ተመልክታለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሪፖርቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የእዳ ቀውስ በአብዛኛዎቹ በድሃ ታዳጊ አገሮች ላይ ያተኮረ በመሆኑ በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ የስርዓት አደጋን ይፈጥራል ተብሎ እንደማይገመት ገልጸዋል።

አክለውም፤ “በዕዳ ጫና እየተሰቃዩ ያሉ ሰዎች እንዲሁም የሕዝብ የዕዳ ጫና በየጊዜው እየጨመረ መምጣት በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡” ብለዋል።

በፈረንጆች 2022 መንግሥታት በሕዝባቸው ሥም የተበደሩት ዕዳ 92 ትሪሊዮን ዶላር እንደነበር የጠቀሱት ዋና ጸሃፊው፤ ይህም የዕዳ መጠን አብዛኛው በታዳጊ አገራት ትከሻ ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ የዕዳ ቀውስ ውስጥ የሚገቡ አገራት ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ በየዓመቱ እያሻቀበ ነው የተባለም ሲሆን፤ በፈረንጆች 2011 22 የነበረው የከፋ የዕዳ ጫና ውስጥ የነበሩት አገራት ቁጥር በፈረንጆች 2022 ላይ 59 መድረሱ ነው የተገልጸው።

ተመድ እንደገለጸው፤ ታዳጊ አገራት እጅግ ከፍተኛ ወለድ በሚያስከፍሉ የግል አበዳሪዎች የእዳ ድርሻቸው እያሻቀበ ነው።

ለአብነት ያህል የአፍሪካ አገሮችን በመጥቀስም፤ የሚከፍሉት አማካይ ብድር አሜሪካ ከምትከፍለው በአራት እጥፍ እንዲሁም የአውሮፓ ሀብታም አገሮች ለተበደሩት ዕዳ ከሚከፍሉት ወለድ በስምንት እጥፍ ይበልጣል ብሏል።

ይህ የዕዳ ቀውስ በተለይ የታዳጊ አገራት መንግሥታትን ለትምህርት፣ ለኃይል፣ ለጤናና ሌሎች መሰረት ልማት ግንባታ ማስፋፊያዎች ገንዘብ አሳጥቷቸዋል ነው የተባለው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የኑሮ ውድነት በተለይ ታዳጊ አገራትን እየተባባሰ ለመጣ የዕዳ ጫና የዳረጉ ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።

እንዲሁም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በብድርና ሌሎች የፋይናንስ አቅርቦቶች ላይ ለበለጸጉና ለታዳጊ አገራት የሚከተሉት ፖሊሲ ኢፍትሃዊ መሆን ሌላኛው ምክንያት መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ተቋማቱ ይህን አሰራራቸውን በማሻሻል የታዳጊ አገራትን ጫና ሊያቀሉ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ከፈረንጆች 2010 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት የአፍሪካ መንግሥታት ዕዳ በሦስት እጥፍ ማደጉም ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “ከባለፈው ሥርዓት ከወሰድነው የኢኮኖሚ ስብራቶች አንዱ ዕዳ ነው፡፡” ሲሉ ጠቅሰው፤ ለውጡ በመጣበት ወቅት (2010) ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 59 በመቶ ድርሻ የነበረው የአገሪቱ የብድር ዕዳ፣ በዚህ ወቅት ወደ 38 በመቶ ዝቅ ማለቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply