36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ ነጻ ንግድ ስምምነት ላይ ይመክራል

አርብ የካቲት 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ የነጻ ንግድ ስምምነትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ በነገው ዕለት የኅብረቱ ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ይጀመራል።

ጉባኤው ከኹለት ዓመት በፊት ሥራ ላይ መዋል የጀመረው “አሕጉር-ዓቀፉ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ” አፈጻጸምና የደረሰበት ደረጃን በዋና አጀንዳነት በመያዝ፣ ግምገማና ውይይት እንደሚያደርግበት የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ሙሉ በሙሉ ሲተገበር ከ98 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከድህነት ሊያላቅቅ ይችላል ያለው ኅብረቱ፣ በአህጉሪቱ 30 ሚሊዮን ዜጐችን ከከፋ ድህነት እንዲሁም 68 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ ከመካከለኛ ደረጃ ወደ ከፍ ያለ የሃብት ደረጃ ያሸጋግራቸዋል ብሏል።

የነጻ ንግድ ቀጠናው ስምምነት ትግበራ ሂደት ሲፋጠንም፣ በፈረንጆቹ 2035 የአህጉሪቱን ገቢ በ450 ቢሊዮን ዶላር ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚገመትም ኅብረቱ አስታውቋል፡፡

በ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ፣ ኮሞሮስ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነትን ከሴኔጋል የምትረከብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የኮሞሮሱ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ ከሴኔጋሉ መሪ ማኪ ሳል የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነትን ይረከባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በነገው ዕለት በሚጀመረውና ዕሁድ ማምሻውን በሚጠናቀቀው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው።

ከመሪዎቹ ጉባኤ ቀደም ብሎም ትናንትና እና ከትናንት በስተያ 42ኛው የኅብረቱ ሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ መካሄዱ ይታወቃል።

The post 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ ነጻ ንግድ ስምምነት ላይ ይመክራል first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply