391 የሚደርሱ በሕገወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው መዘጋቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በባንክ ቤቶች ውስጥ ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም በዚህ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ እንዳሉ ተገልጿል

አርብ መስከረም 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ብሔራዊ ባንክ 391 የሚደርሱ ሕገወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው ተዘግቶ ክስ የመመስረት ሂደት እንደተጀመረ አስታወቀ።

በሕገ ወጥ መልኩ በጥቁር ገበያ ላይ በተሠማሩ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጉዳዩን አስመልክተው በሂልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ 391 የሚደርሱ ሕገ ወጥ የሐዋላ አገልግሎት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው መዘጋቱን ተናግረዋል።

ባንኩ የግለሠቦቹን ሥም ዝርዝር ለፍትሕ ሚኒስቴር በመላክ ክስ የመመስረት ሂደት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በባንክ ቤቶች ውሥጥ ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም በዚህ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትም እንዳሉ ጠቅሰው፤ በነዚህ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃና ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ይሕን ሕገወጥ ድርጊት ለሚጠቁሙ ዜጎች የወሮታ አከፋፈል ስርዓት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከተፈቀደው በላይ በቤት ውስጥ የብር ክምች የሚያደርጉ፣ የሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን የሚሠሩና የሚያሠራጩ አካላት እንዲሁም በሕገወጥ መልኩ የሐዋላ አገልግሎት የሚሠጡ ወይም በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለሚጠቁሙ ዜጎች ደህንነታቸውና ሚስጥራዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ የሚሸልምና ወረታውን የሚከፍል መሆኑን ማስታወቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የፈቀደውን የፍራኮ ቫሉታ ፍቃድ እንደ እድል በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ ዶላር በመጠቀም ሸቀጦችን የማስገባት ተግባር የተስተዋለ በመሆኑ፤ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የባንክ ማስረጃ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

The post 391 የሚደርሱ በሕገወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው መዘጋቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply