4ኛው የመላው አፍሪካ ድህረ-ምርት ኮንግረስና ኤግዚቢሽን ተካሄደ

4ኛው የመላው አፍሪካ ድህረ-ምርት  ኮንግረስና ኤግዚቢሽን ተካሄደ

”በኢትዮጵያ የድህረ-ምርት ብክነቱ ወደ 25 ሚ. ገደማ ህዝብ የሚመግብ ነው“

ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዳራሽ የተከፈተው አራተኛው የመላው አፍሪካ ድህረ-ምርት ኮንግረስና ኤግዚቢሽን፣ ”ዘላቂ የድህረ-ምርት አመራር፡ የአፍሪካን የእርስ በእርስ የግብርና ንግድ ማሳደግና የምግብና ሥነምግብ ዋስትናን ማጎልበት“ በሚል ጭብጥ፣ እስከ ትላንት  አርብ  ድረስ ለአራት ቀናት ተካሂዷል፡፡  
ኮንግረሱ በአፍሪካ አህጉር እጅግ ወሳኝ የሆነውን የምግብና ውሃ ብክነት ችግር መፍትሄ ለማበጀት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በኮንግረሱ ላይ ለውይይት ከቀረቡ ርዕሰጉዳዮች መካከል፡- ዘላቂ የድህረ-ምርት አሰራሮች፣ የምርት ብክነትን የሚቀንሱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ብክነትን ለመከላከል የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማስፋት አጋርነትን ማጠናከር የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በኮንግረሱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ ኮሚሽነሯ ክብርት ጆሴፋ ሊዎኔል ኮሬያ ሳኮ፤ “በዓለማቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ብናደርግም፣ የእህል ብክነት በተለይም የድህረ-ምርት ብክነት በአፍሪካ የልማት ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፤ ይሄ ደግሞ  የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ  ችግርን ያባብሳል፣ የገበሬዎችንና ማህበረሰቦችን ገቢ ይቀንሳል፣ ውዱን የመሬት፣ ውሃና ኢነርጂ ሃብትን በከንቱ እንዲባክን ያደርጋል..” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብና ሥነ-ምግብ ተባባሪ ፕሮፌሰር አሻግሬ ዘውዱ (ዶ/ር) በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ድህረ ምርት ብክነት በእህል እስከ 30%፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ እስከ 70% እንደሚደርስ ጠቁመው፤ የምርት ብክነቱ ወደ 25 ሚሊዮን ገደማ ህዝብ የሚመግብ ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን ምርታችንን እርስ በርስ ስለማንገበያይ ከፍተኛ ብክነት ይከሰታል የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ እስያውያን እስከ 60% ድረስ ሲገበያዩ፣ አፍሪካውያን ግን እስከ 20% ብቻ ነው የሚገበያዩት፤ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የምግብ ብክነት ዓለማቀፍ ክስተት እንደመሆኑ መጠን፣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ ለሰው ልጅ ፍጆታ ከሚመረተው ምግብ 30 በመቶ ገደማ የሚሆነው በከንቱ ይባክናል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) እ.ኤ.አ በ2019 ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የምግብ ብክነቱ በገንዘብ ሲመነዘር፣ በበለጸጉት አገራት በየዓመቱ ወደ 680 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን፤ በታዳጊ አገራት ደግሞ 310 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያህል ተገምቷል፡፡  
አራተኛውን የመላ አፍሪካ ድህረ-ምርት ኮንግረስና ኤግዚቢሽን፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከተለያዩ የልማት አጋሮች፣ የግል ዘርፉ ተዋናዮች፣ የምርምር ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ታውቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply