451 የፖስታ ቤት ሰራተኞች ለምን ተባረሩ?

128 አመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በተለያዩ ምክንያቶች 451 ያህል ሰራተኞች ከስራ ቀንሷቸዋል፡፡

ከስራ የተቀነሱት ሰራተኞች መስራቤቱን ቢያንስ ከ20 አመት በላይ ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ሰራተኞች የስራ እድገት እና ደሞዝ ጭማሪ ስንጠብቅ ጭራሽኑ ከስራችን ተሰናብተናል ሲሉ ለጣበያችን ተናግረዋል፡፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ ፖስታ ቤት በስሩ ቀጥሯቸው መስራቤቱን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ያገለገሉ ሰራተኞች ከመዋቅር ከትምህርት ዝግጅት እና በስነምግባር ግድፈት ምክንያት ከ450 በላይ ሰራተኞች ተቀናሽ እንዲሆኑ እድርጓል ነው የተባለው፡፡

ከመስራቤቱ ከተሰናበቱ ሰራተኞች መካከል ከጉልበት ስራ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ባለሙያ ድረስ ያሉ ሰራተኞች ይገኙበታል፡፡

ከሰርተፍኬት እስከ ዲግሪ ድረስ ያላቸው ሰራተኞችም መሰናበታቸውን ነው ጣበያችን ያነጋገራቸው ቅሬታ አቅራቢዎች የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ካሰናበታቸው ሰራተኞች መካከል አብዛኛዎቹ ከ20 አመት በላይ ማገልገላቸውን ይናገራሉ፡፡

ውሳኔው በሀገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የተቆጠርን መስሎናል ሲሉ ቅረታቸውን እንዲህ ነግረውናል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ምን ምላሽ ሰጠ?

ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የማርኬቲንግ እና የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ በላይ ማሙሽ እንደተናገሩት የሰራተኞቹ ስንብት ከህግ ውጭ የሆነ አይደለም ብለዋል፡፡

ከተቋሙ የተቀነሱት ሰራተኞች በተለያዩ ጊዜያት የስነምግባር ግድፈት የፈጸሙ የስራ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ሆኖ በመገኝቱ እና ከብቃት ማረጋጋጫ ሲኦሲ ማምጣት ባለማቻላቸው ነው ብለዋል፡፡

ላለፉት ሁለት አመታት በሰራተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ውይይት ተደርጓል ያሉት ሃላፊው ሁሉም ስራ የተሰራው በህግ እና በህግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ከመጋቢት 2013 ዓ.ም ወዲህ የኢትዮጵያ ፖስታ” የሚል አዲስ መለያውን ያስተዋወቀው ድርጅቱ፤ በርካታ የማሻሻያ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ በላይ ተናግረዋል፡፡

እያስተካከላቸው ከሚገኙ ስራዎች መካከል አሰራሩን ወደ ዲጂታል የማዘመን አሰራር ይገኝበታል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply