You are currently viewing 5.2 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የፌደራል መንግስት ቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት፤ የአዋጭነት ጥያቄ ቀረበበት

5.2 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የፌደራል መንግስት ቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት፤ የአዋጭነት ጥያቄ ቀረበበት

በተስፋለም ወልደየስ

የፌደራል መንግስት ለ2017 ካዘጋጀው በጀት ውስጥ፤ 5.2 ቢሊዮን ብር ያህሉን ለቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት መመደቡ የአዋጭነት ጥያቄ አስነሳ። የቢሮዎች ግንባታ መንግስት ለኪራይ የሚያወጣውን “ከፍተኛ ወጪ” እንደሚያድን የገለጸው የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ፕሮጀክቱ “እንደሌሎቹ ሴክተሮች የአዋጭነት ጥናት ተረጋግጦ የሚኬድበት አይደለም” ብሏል።

የመንግስት ቢሮዎች ግንባታ ጉዳይ ጥያቄ የተነሳበት ትላንት ሰኞ ሰኔ 17፤ 2016፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ የበጀት ውይይት ላይ ነው። ውይይቱን የጠራው የምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው 12 ጥያቄዎችን አዘጋጅቶ ነበር።  

የቋሚ ኮሚቴው አባል በሆኑት ዶ/ር ሚልኪያስ አየለ አማካኝነት በንባብ ከቀረቡት ከእነዚህ ጥያቄዎች የመጨረሻው፤ ለመንግስት ቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት “የቅድመ ግንባታ የአዋጭነት ጥናት” መከናወኑን ያጠየቀ ነበር። ዶ/ር ሚልኪያስ የግንባታ ፕሮጀክቱ “አግባብነት ካለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአዋጭነት ማረጋገጫ ሰነድ ወይም ሰርተፍኬት” ስለመሰጠቱም ማብራሪያ ጠይቀዋል።

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

የፓርላማ አባሉ ከዚህ በተጨማሪም የግንባታ ፕሮጀክቱን እንዲያስፈጽም በጀት በተመደበለት በከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ላይ ያላቸውን ጥያቄ ሰንዝረዋል። ዶ/ር ሚልኪያስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቢሮዎቹን ለመገንባት የሚያስችል “የሰው፣ የቴክኖሎጂ እና የአደረጃጀት አቅም መፍጠሩ” ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ በመጠየቅ የውይይት መድረኩን ለገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ለቅቀዋል።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ፤ “የመንግስት ቢሮ ኪራይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ” መምጣቱን በመጥቀስ የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት አብራርተዋል። “በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የቢሮ ኪራይ እየከፈልን ነው። ተመኑም፣ ዋጋውም፤ ከሌሎችም ነገሮች ጋር ታሳቢ እየተደረገ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ አለ” ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል።

የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮ በሚከራዩበት ወቅት “ለስራ አስፈላጊ የሆኑ” የኢንፎርሜሽን ቴከኖሎጂ ሲስተሞችን እንደሚዘረጉ ያስታወሱት አማካሪው፤ ለዚህ የሚወጣው ገንዘብ “ለብክነት እንዳይዳረግ” እና “በዘለቄታዊነት እንዲቀጥል” ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም የፌደራል መንግስት ለመስሪያ ቤቶች ቢሮ ግንባታ ባለፉት ዓመታት በጀት ሲመድብ መቆየቱንም አመልክተዋል።

የፌደራል መንግስት “በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመስሪያ ቤቶች የቢሮ ኪራይ ወጪ ለመቀነስ እና ምቹ የስራ ሁኔታን ለማመቻቸት” በሚል ምክንያት፤ በ2014 ለቢሮዎች ግንባታ የመደበው በጀት 2.2 ቢሊዮን ብር ነበር። ግንባታዎቹን በማዕከል የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፤ በቀጣዩ ዓመትም ተመሳሳይ መጠን ያለው በጀት እንዲመደብለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ሆኖም የገንዘብ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ድልድልን ሲያደርግ ለፕሮጀክቱ የፈቀደው የገንዘብ መጠን ወደ 1.78 ቢሊዮን ብር ዝቅ ብሏል። በተከታዩ ዓመትም ቢሆን፤ የቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክቱ የተመደበለት የገንዘብ መጠን ቀድሞ ከነበሩት ሁለት ዓመታት ያነሰ ነው። ለመንግስት ቢሮዎች እና መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፤ በዘንድሮው የ2016 በጀት የተመደበው በጀት 1.6 ቢሊዮን ብር ነበር።

ለፕሮጀክቱ የተመደበው የገንዘብ መጠን፤ በቀጣዩ 2017 በጀት ዓመት በ3.6 ቢሊዮን ብር ይጨምራል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ225 ፐርሰንት የጨመረው የቢሮዎች ግንባታ በጀት የአዋጭነት ጥያቄ ቢነሳበትም፤ በዚህ ረገድ “ስጋት ሊኖር” እንደማይገባ የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት አማካሪው በትላንቱ የፓርላማ ስብሰባ ማስተማመኛ ሊሰጡ ሞክረዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“የቢሮ ኪራይ ከአዋጅ አኳያ፤ ከፕሮጀክት አኳያ የሚታይ ነው። በአዋጭነት ጥናት አይደለም። አስፈላጊነቱ ይታወቃል። በቢሮ ኪራይ ሊኖር የሚችለው ወጪ እና ቢሮ በመስራት የምናድነው ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ልዩነት አለው” ሲሉ አቶ ተፈሪ ለፓርላማ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል።  

“የቢሮ አስፈላጊነቱ በመንግስትም ታምኖበት በሚመለከተው አካል ‘ኮንሰፕት ኖት’ እየተዘጋጀለት በዚያ ደረጃ የሚታይ ነው እንጂ፤ እንደሌሎቹ ሴክተሮች የአዋጭነት ጥናት ተረጋግጦ የሚኬድበት አይደለም። ራሱ ‘ጀስቲፋይ’ የሚያደርገው ነገር አለ” ያሉት የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ፤ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ “የተሻለ የበጀት መጠን” መመደብ እና “የበለጠ መስራትን” የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል። 

“በተበጣጠሰ መልኩ ከምንሰራ ወደፊት እንደውም፤ በማዕከል ቢሮ የምንገነባበት ሁኔታ ማየት ይፈልጋል። በሰፊው፣ በክላስተርም ቢሆን ያንን መንገድ መከተል አለብን” ሲሉም አቶ ተፈሪ አሳስበዋል። መንግስት ለቢሮ ግንባታ የመደበውን በጀት “ሊያሰራ የሚችል አቅም መፍጠሩን” በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም አማካሪው በማብራሪያቸው ማጠቃለያ ምላሽ ሰጥተዋል። 

“የቢሮ አስፈላጊነቱ በመንግስትም ታምኖበት በሚመለከተው አካል ‘ኮንሰፕት ኖት’ እየተዘጋጀለት በዚያ ደረጃ የሚታይ ነው እንጂ፤ እንደሌሎቹ ሴክተሮች የአዋጭነት ጥናት ተረጋግጦ የሚኬድበት አይደለም”

– አቶ ተፈሪ ደመቀ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ

“በከተማ እና መሰረተ ልማት [ሚኒስቴር] ራሱን የቻለ፣ ሙያው የሚፈልገው አደረጃጀት እና የሰው ኃይል ተመድቦበት እየተሰራበት ነው። በዚህ ዓመት እንኳን በከፍተኛ ደረጃ በተጨማሪ በጀትነት ካስተናገድናቸው መስሪያ ቤቶች [አንዱ] የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ነው” ሲሉም ፕሮጀክቱ “ቅድሚያ እና ትኩረት” ተሰጥቶ  እየተከናወነ ያለ መሆኑን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply