56 ሺሕ ተማሪዎች በቀጣይ ኹለተኛ ዙር ፈተና እንደሚዘጋጅላቸው ተገለጸ

ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በተለያዩ አካባቢዎች ከሰላምና ፀጥታ ጋር ተያይዞ መፈተን የማይችሉና ከአገር የወጡ የኮሚኒቲ ተማሪዎች በአጠቃላይ 56 ሺሕ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በቀጣይ ኹለተኛ ዙር ፈተና እንደሚዘጋጅላቸው የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ2014 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናን ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጸ ሲሆን፤ ፈተና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

ባለፉት 6 ዓመታት ከፈተና ስርቆትና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ጋር ተያይዞ ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ችግር ገጥሞት የነበረ በመሆኑ፤ ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተፈታኞች ከቀጣይ ሰኞ ጀምሮ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲፈተኑ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ ዘንድሮ ከ 900 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ለፈተና የሚቀመጡ በመሆኑ ይህንን ቁጥር በአንድ ጊዜ ማስተናገድ አለመቻሉ ተገልጿል።

ስለዚህም የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከመስከረም 26-28 ወደሚፈተኑባቸው ዩንቨርሲቲዎች የሚገቡ ሲሆን፤ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 02 ፈተና ወስደው ከጥቅምት 03 ጀምሮ ወደመጡበት እንደሚመለሱ ተጠቅሷል።

በሁለተኛ ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከጥቅምት 5 አስከ ጠቅምት 6 ወደ ዩንቨርሲቲዎች የሚገቡ ሲሆን ከጥቅምት 8 እስከ ጠቅምት 11 ፈተና ወስደው ከጥቅምት 12 ጀምሮ ወደመጡበት የሚመለሱ ይሆናል ተብሏል።

ተማሪዎች ለፈተና ሲመጡ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እና ሌሎችም ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ቁሶችን መያዝ እንደማይችሉ መጠቆሙን ኢብኮ ዘግቧል።

ተማሪዎችን ወደ ተመደቡባቸው አካባቢዎች የሚያደርሷቸው የክልል የፀጥታ አካላት ሲሆኑ፤ በዩኒቨርሲቲዎች የጥበቃና ፍተሻ ሥራን የሚሰሩት የፌዴራል ፖሊስ አባላት መሆናቸውንም የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

The post 56 ሺሕ ተማሪዎች በቀጣይ ኹለተኛ ዙር ፈተና እንደሚዘጋጅላቸው ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply