8ተኛው ሀገር አቀፍ የጤና ክብካቤ ጥራት አመታዊ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባኤው እየተካሄደ የሚገኘው “የጤና አገልግሎት ጥራት፣ደህንነትና ፍትሀዊነትን ለማሻሻል የጤና ስርአት ኢኖቬሽን ማጎልበት” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡

ጉባኤው ከዛሬ የካቲት 26 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 28/2016 ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ጉባኤ የጤና አገልግሎት እና ጥራትን ለማሻሻል የሚረዳ እና 6 መቶ 50 የሚሆኑ ተሳታፊዎች በአካል የተገኙበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ጉባኤው በሚኖረው ቆይታ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የጤና ስርአት የሚሰጠውን አገልግሎት ስለማሻሻል፤የጤና ስርዓቱ ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ሁሉም ዜጋ አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ስርዓት መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛው በዚህ ጉባኤ የሚማር፣መረጃ የሚስብስብ ፣ አዳዲስ ስርአቶችን የሚቀበል እና ለለውጥ ዝግጁ የሆነ በአጠቃላይ የተስተካከል የጤና ስርዓት መፍጠር ላይ ያተኮሩ በሳል ምክክሮች እንደሚካሄዱ ጠቅሰው ጉባኤው ሲጠናቀቅ በቀጣይ በዘርፉ ሊሻሻሉና ሊጠናከሩ የሚገባቸውን አሰራሮች በጉልህ ያመላክታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት ከፍተኛ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትና ጥራት መሻሻሎችን ማስመዝገቧን ጥናቶች ያሳያሉ።

ሆኖም አሁንም ከ110 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ፈተና ሆኖ መቀጠሉ ይነሳል፡፡

ተላላፊ በሽታዎች፣ የንፁህ ውሃ እጥረት፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ጉድለት እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሃገሪቱ በጤናው ዘርፍ ለማሳካት የምትሰራቸውን ስራዎችን እየፈተኑ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሐመረ ፍሬው
የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply