
83ኛውን የአገው ፈረሰኞች ዓመታዊ ክብረ በዓል በአገው ባህል መሠረት እንግዶች ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የአዊ ብሄ/አስ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 19 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በዓሉን በተመለከተ የአዊ ብሄ/አስ ባህልና ቱሪዝም እና የአዊ ብሄ/አስ መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሀላፊዎች በጋራ መግለጫ ሰጠዋል። የብሄ/አስ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ አቶ ለይኩን ሲሳይ እንደገለፁት የዘንድሮው የአገው ፈረሰኞች በዓል በተለየ መንገድ ለማክበር ቀደም ተብሎ ዝግጅቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ማህበሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በቅርስነት መመዝገቡን ያነሱት ሀላፊው በዩኒስኮ እንዲመዘገብ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። የፊታችን ከጥር 20-23/2015 ዓ.ም የሚከበረው ክብረ በዓል በዩኒስኮ ለመመዝገብ በሚያስችል ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር በመግለጫቸው ተናግረዋል። በዓሉ የአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን አዊ ተዝቆ የማያልቅ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴቶችን የሚተዋወቁበት በዓል እንደሆነም አመላክተዋል። የአዊ ህዝብና ፈረስ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ለይኩን በዓሉን ስናከብር የአዊን የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ባህላዊ ምምግብ፣አልባሳት፣ጭፈራውን በአጠቃላይ የአገውን ባህል፣ወግ፣ ቋንቋና ታሪክ አካተን የምናስተዋውቅበት እንደሆነም በመግለጫው ተነስቷል። አያይዘውም በተያያዘ በእንጅባራ እና አካባቢው ያሉ የተፈጥሮ መስህቦችን ለመጡ እንግዶች በእግረመንገዱ የምናስጎበኝበት መርሃ ግብር እንዳለም ነው የገለፁት። የሆቴሎች ዝግጅት በተመለከተም ከእንጅባራ ከተማ በተጨማሪ በቅርብ እርቀት የሚገኙ ከተሞችም የአገው ባህልን በጠበቀ መንገድ ለእንግዶች የመኝታ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ለይኩን አስታውቀዋል። የአዊ ብሄ/አስ መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሀላፊወ/ሮ ትግስት መኩሪያ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በ2ቀናት ብቻ ይካሄድ የነበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል ዘንድሮ ከጥር 20ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። የፈረሰኞች መወድስ ቅኔ፣ባህል ዘመናዊ ፋሽን ሾው፣የልጃገረዶች የቁንጅና ውድድር የባህላዊ ቁሳቁሶች ኤግዚቢሽን ፣የታሪካዊ አብያተክርስቲያናት ንግስ ፣የሩጫ ውድድር ፣የአርሶአደሮች የሙዚቃ ፌስቲቫል እና የጎዳና ላይ የፈረስና የሙዚቃ ትርኢቶች እስከ ጥር 22 የሚካሄዱ መሆናቸውን ሀላፊዋ ገልፀዋል። በዋናው በዓል ጥር 23 የፈረስ ትርኢቶች ጨምሮ ልዩ ልዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱ የተናገሩት ወ/ሮ ትግስት ፕሮግራሙ በአሚኮ ቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል ነው ያሉት። ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ታዋቂ ሰዎች፣አርቲስቶች እና ሚዲያዎች ይገኛሉ። ከዛሬ ጀምሮም እንጅባራ ከተማን ለማስዋብ የፅዳት ዘመቻ እንደተካሄደም ነው የገለፁት። በበየአዊ ብሄ/አስ 83ኛውን የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን በአገው ባህል መሠረት እንግዶቹን ለመቀበል ሙሉ ዝግጀት ማድረጉን ተናግረዋል ሲል አዊ ኮሚዩኒኬሽን ዘግቧል።
Source: Link to the Post