Updateየሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በከፊል ስራ መጀመሩ ተሰማ፡፡በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፤ ሐዲያ ዞን ሾኔ ከተማ የሚገኘዉ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በከፊል ስራ መጀመሩን የ…

Update

የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በከፊል ስራ መጀመሩ ተሰማ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፤ ሐዲያ ዞን ሾኔ ከተማ የሚገኘዉ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በከፊል ስራ መጀመሩን የሆስፒታሉ የተኝቶ ታካሚዎች ክፍል አስተባባሪ ዶ/ር ፋብዩ አየለ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፤ ሐዲያ ዞን ሾኔ ከተማ ፣ ላለፉት 3 ወራት የተቋረጠባቸው ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ተከትሎ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸዉ ተገልጾ ነበር፡፡

ከ500 በላይ የሚሆኑ የሆስፒታሉ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ላይ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በትናንትናዉ ዕለትም በዚህ ጉዳይ ከከተማዉ ከንቲባ ጋር መነጋገራቸዉን ዶ/ር ፋብዩ ነግረዉናል፡፡

ከከንቲባዉ ጋር በነበራቸዉ ቆይታም ‹‹እየሰራችሁ ጠይቁ››መባላቸዉን ያነሱት ዶ/ር ፋብዩ፤ያንን በማሰብ የህጻናት እና የአዋቂ ደንገተኛ ክፍሎችን እና የእናቶች ማዋለጃ ክፍሎችን ከፍተዉ በከፊል ስራ መጀመራቸዉን ገልጸዋል፡፡

ከከንቲባዉ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ላለፉት 3 ወራት ከተቋረጠባቸዉ ደሞዝም የነሀሴ ወር ቀሪ ክፍያ በዛሬዉ ዕለት እንደተከፈላቸዉ ያነሱት አስተባባሪዉ ፤አሁን ላይ የ2 ወር ደሞዝ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣የ2015 ዓም የጥቅምት ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲሁም የ2012 ዓም የ2 ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንደሚቀር ነግረዉናል፡፡

እኛ የድንገተኛ እና የማዋለጃ ክፍሎችን ከፍተን በከፊል ስራ ስንጀምር ያልተከፈለ ቀሪ ክፍያዎችን ለመጠየቅ የተመረጡ ሰራተኞች ወደ ሆሳዕና እና ወራቤ ሄደዋል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ለቀጣዩም ማስተማመኛ የለንም ያሉት ዶ/ር ፋብዩ ‹‹ዛሬ 15 ነዉ ፤በቀጣይ ከ15 ቀናት በኋላ ደግሞ መልሶ ወር ይመጣል፤ ይሄኛዉን ተበድረዉ ከፈሉ ፤ቀጣይስ ማን ነዉ የሚከፍለዉ? ማነዉ ባለቤት? የሚለዉን ለማወቅ ተመካክረን የተወሰኑት ወደ ክልል ሄደዋል የተወሰኑት ደግሞ እዚህ ሆስታሉን በከፊል ከፍተን እየሰራን ነዉ፤ ዛሬ ምላሽ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፤ ስለዚህ የሚመጣዉን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለውናል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube
https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/video

Source: Link to the Post

Leave a Reply